2 ዜና መዋዕል 25:15-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. የእግዚአብሔርም ቊጣ በአሜስያስ ላይ ነደደ፤ ነቢይንም ላከበት፤ ነቢዩም፣ “የገዛ ሕዝባቸውን ከእጅህ ማዳን ያልቻሉትን የአሕዛብን አማልክት ርዳታ የጠየቅኸው ለምንድን ነው?” አለው።

16. እርሱም በመናገር ላይ ሳለ፣ ንጉሡ፣ “ለመሆኑ አንተን የንጉሥ አማካሪ አድርገን ሾመነሃልን? ዝም አትልም እንዴ! መሞት ትፈልጋለህ?” አለው።ነቢዩም ዝም አለ፤ ሆኖም፣ “ይህን አድርገሃልና ምክሬንም አልሰማህምና፤ እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንደወሰነ ዐውቃለሁ” አለ።

17. የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ አማካሪዎቹን ካማከረ በኋላ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዩ የልጅ ልጅ፣ የኢዮአካዝ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ኢዮአስ፣ “እስቲ ናና ፊት ለፊት እንጋጠም” ሲል ላከበት።

18. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ ግን፣ ለይሁዳ ንጉሥ ለአሜስያስ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “አንድ የሊባኖስ ኵርንችት፣ ‘ሚስት እንድትሆነው ሴት ልጅህን ለልጄ ስጠው’ ሲል ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከበት። ከዚያም የዱር አውሬ ከሊባኖስ ወጥቶ ኵርንችቱን ረገጠው።

19. ኤዶምን አሸንፌአለሁ ብለህ ራስህን በትዕቢት ክበኸዋል፤ ኮርተሃልም፤ ግን ዐርፈህ እቤትህ ተቀመጥ! በራስህና በይሁዳ ላይ ውድቀት ታመጣ ዘንድ ችግር የምትጠራው ስለምንድን ነው?”

20. የኤዶምን አማልክት ማምለክ በመፈለጋቸው፣ እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሊሰጣቸው ወስኖአልና፣ አሜስያስ አላዳመጣቸውም።

21. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስ አደጋ ጣለ። እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ በይሁዳ ውስጥ ቤትሳሚስ በተባለ ስፍራ ፊት ለፊት ተጋጠሙ።

22. ይሁዳ በእስራኤል ክፉኛ ተመታ፤ እያንዳንዱም ሰው ወደየመኖሪያው ሸሸ።

23. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ከኤፍሬም በር እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አንድ መቶ ሰማንያ ሜትር ያህል ርዝመት ያለውንም የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ።

24. እርሱም በዖቤድ ኤዶም ጥበቃ ሥር የነበረውንና በቤተ መቅደሱ የተገኘውን ወርቅ፣ ጥሬ ብርና ዕቃ በሙሉ፣ ከቤተ መንግሥቱም ንብረትና በመያዣ ከያዛቸው ሰዎች ጭምር ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

25. የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ፣ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአስ ከሞተ በኋላ አሥራ አምስት ዓመት ኖረ።

26. በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነው ሌላው ተግባር ሁሉ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

27. አሜስያስ እግዚአብሔርን መከተል ከተወ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ስላመፁበት ወደ ለኪሶ ሸሸ፤ ነገር ግን የሚከታተሉትን ሰዎች ከኋላው ልከው በዚያው በለኪሶ ገደሉት።

28. በፈረስ ተጭኖ ከመጣ በኋላም፣ እንደ አባቶቹ ሁሉ በይሁዳ ከተማ ተቀበረ።

2 ዜና መዋዕል 25