1. ከዐረቦች ጋር ወደ ሰፈር የመጡት ወራሪዎች፣ ታላላቅ ወንድሞቹን ሁሉ ገድለዋቸው ስለ ነበር፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ የኢዮሆራምን የመጨረሻ ልጅ አካዝያስን በአባቱ ምትክ አነገሡት። ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ መግዛት ጀመረ።
2. አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የዘንበሪ የልጅ ልጅ ነበረች።
3. እናቱ ክፋትን እንዲያደርግ ትመክረው ስለ ነበር፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ።
4. ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለ መሩት፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ።
5. እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም የሶርያን ንጉሥ አዛሄል ለመውጋት ወደ ሬማት ገለዓድ በሄደ ጊዜ የእነዚህኑ ሰዎች ምክር ተከትሎ ከኢዮራም ጋር አብሮት ሄደ፣ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት።