1. አብያ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፈንታ ነገሠ፤ በዘመኑም በምድሪቱ ለዐሥር ዓመት ሰላም ሆነ።
2. አሳ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤
3. ባዕዳን መሠዊያዎችንና ማምለኪያ ኰረብታዎችን አስወገደ፤ ማምለኪያ ዐምዶችን አፈረሰ፤ አሼራ ለተባለች ጣዖት አምላክ የቆሙ የዕንጨት ቅርጽ ምስሎችንም ቈራረጠ፤
4. የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ፣ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ የይሁዳን ሕዝብ አዘዘ።
5. ከእያንዳንዱም የይሁዳ ከተሞች የማምለኪያ ኰረብታዎችንና የዕጣን መሠዊያዎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ አገዛዝ ዘመን ሰላም አገኘች።
6. በምድሪቱ ሰላም ስለ ሰፈነ፣ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። እግዚአብሔር ዕረፍት ስለ ሰጠውም፣ በዘመኑ የተዋጋው ማንም አልነበረም።