9. ደግሞስ የአሮን ልጆች የሆኑትን ካህናትና ሌዋውያን አባርራችሁ፣ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ እናንተም የራሳችሁን ካህናት አልሾ ማችሁምን? አንድ ኮርማና ሰባት አውራ በግ ይዞ ራሱን ለመቀደስ የሚመጣ ማናቸውም ሰው አማልክት ላልሆኑ ለእነዚያ ጣዖታት ካህን ይሆናል።
10. “ለእኛ ግን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱንም አልተውንም፤ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ ያሉት ካህናት የአሮን ልጆች ሲሆኑ፣ ረዳቶቻቸውም ሌዋውያኑ ናቸው።
11. እነርሱም በየጧቱና በየማታው የሚቃጠል መሥዋዕትና ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፤ የገጹን ኅብስት በሥርዐቱ መሠረት በነጻው ጠረጴዛ ላይ ያኖራሉ፤ በየማታውም በወርቁ መቅረዝ ላይ ያሉትን ቀንዲሎች ያበራሉ፤ እኛም የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንፈጽማለን፤ እናንተ ግን ትታችሁታል።
12. እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ መሪአችንም እርሱ ነው። መለከት የያዙ ካህናቱም የጦርነቱን ድምፅ በእናንተ ላይ ያሰማሉ። እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ አይቀናችሁምና፣ ከአባቶቻችሁ አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር አትዋጉ።”
13. በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ከሰራዊቱ ከፊሉን ከይሁዳ ሰራዊት በስተ ጀርባ እንዲያደፍጡ ላከ፤ የቀረውም ሰራዊት ከእርሱ ጋር የይሁዳን ሰራዊት ፊት ለፊት እንዲገጥሙ አደረገ።
14. የይሁዳም ሰዎች ዙሪያቸውን ሲመለከቱ ከፊትና ከኋላ መከበባቸውን አዩ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጮኹ፤ ካህናቱም መለከታቸውን ነፉ።
15. የይሁዳም ሰዎች በፉከራ የጦርነት ድምፅ አሰሙ፤ እግዚአብሔር ኢዮርብዓምንና እስራኤልን ሁሉ በአብያና በይሁዳ ፊት ፊጽሞ መታቸው።
16. እስራኤላውያን ከይሁዳ ፊት ሸሹ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው።
17. አብያና ሰዎቹም ከባድ ጒዳት አደረሱባቸው፤ ከዚህ የተነሣም ከእስራኤል ብርቱ ተዋጊዎች መካከል አምስት መቶ ሺህ ሰዎች ተገደሉ።
18. በጦርነቱም የእስራኤል ሰዎች ተዋረዱ፣ የይሁዳ ሰዎች ግን በአባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ታምነዋልና ድል ነሡ።
19. አብያም ኢዮርብዓምን አሳድዶ የቤቴልን፣ የይሻናንና የዔፍሮንን ከተሞች ከነ መንደሮቻቸው ወሰደበት።
20. ኢዮርብዓም በአብያ ዘመን እንደ ገና ሊያንሠራራ አልቻለም፤ ከዚያም እግዚአብሔር ስለ ቀሠፈው ሞተ።
21. አብያ ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ዐሥራ አራት ሚስቶች አግብቶም ሃያ ሁለት ወንዶችና ዐሥራ ስድስት ሴቶች ልጆች ነበሩት።
22. በአብያ ዘመን የተከናወነው ተግባር፣ እርሱ የፈጸመውና የተናገረው ሁሉ በነቢዩ በአዶ የታሪክ መዛግብት ተጽፎአል።