4. በዚህ ጊዜ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ሰው አገልጋይ ግያዝን፣ “ኤልሳዕ ያደረጋቸውን ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ እስቲ ንገረኝ” እያለው ነበር።
5. ኤልሳዕ ልጇን ከሞት ያስነሣላት ሴት ስለ ቤቷና ስለ መሬቷ ለማመልከት ወደ ንጉሡ ዘንድ የቀረበችውም፣ ኤልሳዕ የሞተውን ልጅ እንዴት እንዳስነሣ፣ ግያዝ ለንጉሡ በሚነግርበት ወቅት ነበር።ግያዝም፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕ ከሞት ያስነሣው ልጇም ይህ ነው” አለ።
6. ንጉሡም ስለ ዚሁ ጒዳይ ጠየቃትና ነገረችው።ከዚያም ንጉሡ፣ “የነበራትን ሁሉ እንዲሁም ትታ ከሄደችበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ያለውን የዕርሻዋን ሰብል በሙሉ እንድትመልስላት” ሲል አንድ ሹም አዘዘላት።
7. ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ ታሞ ነበር፤ ለንጉሡም፣ “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል ብለው ነገሩት።
8. እርሱም አዛሄልን፣ “ገጸ በረከት ይዘህ ሂድና የእግዚአብሔርን ሰው ተገናኘው። በእርሱም አማካይነት፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው።
9. አዛሄልም ደማስቆ ካፈራቻቸው ምርጥ ነገሮች ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ይዞ ኤልሳዕን ለመገናኘት ሄደ። ሄዶም እፊቱ ቆመና፣ “የሶርያ ንጉሥ ልጅህ ቤን ሃዳድ፣ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ሲል ወደ አንተ ልኮኛል” አለው።
10. ኤልሳዕም፣ “ሂድና፣ ‘መዳኑንስ በርግጥ ትድናለህ’ በለው፤ ነገር ግን እንደሚሞት እግዚአብሔር ገልጦልኛል” ሲል መለሰለት።
11. እስኪያፍር ድረስም፣ አዛሄልን ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ ከዚያም የእግዚአብሔር ሰው እንባውን አፈሰሰ።
12. አዛሄልም፣ “ጌታዬ የሚያለቅሰው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።ኤልሳዕም መልሶ፣ “በእስራኤላውያን ላይ የምታደርሰውን ጒዳት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጐልማሶቻቸውን በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናታቸውን በምድር ላይ ትፈጠፍጣለህ፤ ያረገዙ ሴቶቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ” አለው።
13. አዛሄልም፣ “ለመሆኑ እንደ ውሻ የሚቈጠር አገልጋይህ ይህን ጀብዱ መፈጸም እንዴት ይችላል?” አለ።ኤልሳዕም መልሶ፣ “መቼም አንተ በሶርያ ላይ እንደምትነግሥ እግዚአብሔር አሳይቶኛል” አለው።
14. ከዚያም አዛሄል ከኤልሳዕ ዘንድ ወጥቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፤ ቤንሀዳድም፣ “ለመሆኑ ኤልሳዕ ምን አለህ?” ሲል ጠየቀው፤ አዛሄልም፣ “በርግጥ ከበሽታህ እንደምትድን ነግሮኛል” አለው።