14. ስለዚህ ሁለት ሠረገሎች ከነፈረሶቻቸው መረጡ፤ ንጉሡም፣ “ሂዱና የሆነውን ነገር እዩ” ብሎ ከሶርያውያን ሰራዊት በኋላ እንዲሄዱ ላካቸው።
15. እነርሱም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከተሏቸው። ሶርያውያን በጥድፊያ ሲሸሹ፣ የጣሉትንም ልብስና ዕቃ በየመንገዱ ላይ ተበታትኖ አገኙ፤ መልክተኞቹም ተመልሰው ይህንኑ ለንጉሡ ነገሩት።
16. ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አንድ መስፈሪያ ማለፊያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸጠ።
17. በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጁን ይደግፈው የነበረውን የጦር አለቃ፣ የቅጥሩ በር ኀላፊ አድርጎት ነበርና በበራፉ መተላለፊያ ላይ ሕዝቡ ሲጋፋ ረጋገጠው፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው ንጉሡ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አስቀድሞ እንደ ተናገረውም የጦር አለቃው ሞተ።