2 ነገሥት 6:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የነቢያት ማኅበር ኤልሳዕን እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፣ በፊትህ የምንቀመጥበት ስፍራ ጠቦናል፤

2. ስለዚህ ወደ ዮርዳኖስ ሄደን፣ እያንዳንዳችን ምሰሶ ቈርጠን እናምጣ፣ በዚያም የምንቀመጥበትን መኖሪያ እንሥራ።”እርሱም፣ “ይሁን ሂዱ” አላቸው።

3. ከመካከላቸውም አንዱ፣ “አንተስ ከአገልጋዮችህ ጋር አትመጣምን?” አለው።ኤልሳዕም፣ “እሺ እሄዳለሁ” አለ፤

4. አብሮአቸውም ሄደ። ወደ ዮርዳኖስም ሄደው ዛፎች መቊረጥ ጀመሩ።

5. ከእነርሱም አንዱ ዛፍ እየቈረጠ ሳለ፣ መጥረቢያው በሮ ከውሃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም፣ “አየ ጒድ ጌታዬ፤ የተውሶ መጥረቢያ እኮ ነው!” ብሎ ጮኸ።

6. የእግዚአብሔርም ሰው፣ “በየት በኩል ነው የወደቀው?” ሲል ጠየቀ። ቦታውን ባሳየውም ጊዜ ኤልሳዕ እንጨት ቈርጦ ወደ ውሃው ውስጥ በመጣል መጥረቢያውን እንዲንሳፈፍ አደረገው።

7. ከዚያም፣ “በል አውጣና ውሰደው” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘርግቶ ወሰደው።

2 ነገሥት 6