19. ኢዮስያስም በቤቴል እንዳደረገው ሁሉ በሰማርያም ከተሞች ኰረብቶች ላይ የእስራኤል ነገሥታት አሠርተዋቸው የነበሩትንና እግዚአብሔርን ያስቈጡበትን ቤተ ጣዖቶች ሁሉ አስወገደ፤ አረከሳቸውም።
20. ኢዮስያስ እነዚያን የየኰረብታውን ማምለኪያ ቦታ ካህናትን ሁሉ፣ በየመሠዊያው ላይ ዐረዳቸው፤ በመሠዊያዎቹ ላይ የሰው ዐፅም አቃጠለ፣ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
21. ንጉሡም መላውን ሕዝብ፣ “በዚህ በኪዳኑ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ፋሲካ አክብሩ” ብሎ አዘዘ።
22. እስራኤልን ከመሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ፣ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ፣ እንደዚህ ያለ ፋሲካ መቼም ተከብሮ አያውቅም።