1. ከዚያም ንጉሡ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠራ።
2. የይሁዳን ሰዎች ሁሉ፣ የኢየሩሳሌምን ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ፣ ካህናቱንና ነቢያቱን ሁሉ ከልጅ እስከ ዐዋቂ አንድም ሰው ሳይቀር ይዞአቸው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መጣ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የተገኘውንም የኪዳኑን መጽሐፍ ቃል በጆሮአቸው እንዲሰሙት በሙሉ አነበበላቸው።
3. ንጉሡም በዐምደ ወርቁ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እግዚአብሔርን እንደሚከተል ትእዛዞቹን፣ ደንቦቹን፣ ሥር ዐቶቹን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹምም ነፍሱ እንደሚጠብቅ፣ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን ኪዳን እንደሚያጸና በእግዚአብሔር ፊት ኪዳኑን አደሰ፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ ለኪዳኑ ያላቸውን ታማኝነት አረጋገጡ።
4. ንጉሡም ለበኣል፣ ለአሼራና ለሰማይ ከዋክብት ሰራዊት ሁሉ የተሠሩትን የመገልገያ ዕቃዎች በሙሉ፣ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንዲያወጡ ሊቀ ካህናቱን ኬልቅያስን በሁለተኛ ማዕረግ ያሉትን ካህናትና የቤተ መቅደሱን በር ጠባቂዎች አዘዘ። ዕቃዎቹንም ከኢየሩሳሌም ውጭ በቄድሮን ሸለቆ ሜዳ ላይ አቃጠላቸው፤ ዐመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።