2 ነገሥት 14:15-29 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. በዮአስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያደረገው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

16. ዮአስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

17. የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።

18. በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

19. አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሴራ ስለጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ላኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉት ሰዎች ወደዚያው ልከው አስገደሉት፤

20. ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ መጥቶ በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።

21. ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት።

22. አሜስያስ ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ ነበር።

23. የኢዮስያስ ልጅ አሜስያስ በይሁዳ በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት፣ የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ ነገሠ፤ አርባ አንድ ዓመትም ገዛ።

24. በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልተመለሰም።

25. የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በጋትሔፌር ነቢይ፣ በአማቴ ልጅ በባሪያው በዮናስ አማካይነት እንደ ተናገረው፣ ከሐማት መተላለፊያ አንሥቶ እስከ ሙት ባሕር ድረስ የነበረውን የእስራኤልን ድንበር ያስመለሰ ኢዮርብዓም ነው።

26. ባሪያም ይሁን ነጻ ዜጋ፣ በእስራኤል የሚኖር ሁሉ እንዴት እጅግ ይሠቃይ እንደ ነበር እግዚአብሔር አየ፤ የሚረዳቸውም አልነበረም።

27. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የእስራኤልን ስም ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋ ስላልተናገረ፣ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም አማካይነት ታደጋቸው።

28. በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ የፈጸመው ሁሉና ያደረጋቸው ጦርነቶች እንዲሁም የይሁዳ ግዛት የነበሩትን ደማስቆንና ሐማትን እንዴት ለእስራኤል እንዳስመለሰ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

29. ኢዮርብዓም ከአባቶቹ ከእስራኤል ነገሥታት ጋር አንቀላፋ፤ ልጁ ዘካርያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

2 ነገሥት 14