2 ነገሥት 14:13-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. የእስራኤል ንጉሥ ዮአስም የአካዝያስን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአስን ልጅ የይሁዳን ንጉሥ አሜስያስን ቤትሳሚስ ላይ ማረከው። ከዚያም ዮአስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ከኤፍሬም ቅጥር በር አንሥቶ የማእዘን ቅጥር በር እስከተባለው ድረስ ርዝመቱ አራት መቶ ክንድ የሆነውን ቅጥር አፈረሰ።

14. በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች ያለውን ወርቅና ብር በሙሉ በዚያም የተገኘውን ዕቃ ሁሉ በመውሰድ ምርኮኞችንም ይዞ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።

15. በዮአስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር፣ ያደረገውና የፈጸመው ሁሉ በይሁዳ ንጉሥ በአሜስያስ ላይ ያደረገው ጦርነት ጭምር በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

16. ዮአስ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮርብዓምም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

17. የኢዮአስ ልጅ የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም የእስራኤል ንጉሥ የኢዮአካዝ ልጅ ዮአስ ከሞተ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ።

18. በአሜስያስ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

19. አሜስያስ በኢየሩሳሌም ሴራ ስለጠነሰሱበት ሸሽቶ ወደ ላኪሶ ሄደ፤ እነርሱ ግን የሚከታተሉት ሰዎች ወደዚያው ልከው አስገደሉት፤

20. ሬሳውም በፈረስ ተጭኖ መጥቶ በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም ተቀበረ።

21. ከዚያም የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የሆነውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት።

22. አሜስያስ ከአባቶቹ ጋር ካንቀላፋ በኋላ ኤላትን እንደ ገና ሠርቶ ወደ ይሁዳ የመለሳት ይኸው ዓዛርያስ ነበር።

2 ነገሥት 14