2 ነገሥት 10:25-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. ኢዩ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ ጠባቂዎቹንና የጦር አለቆቹን፣ “ግቡና ግደሏቸው፤ ማንም እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ። እነርሱም በሰይፍ ፈጇቸው፤ ጠባቂዎቹና የጦር ሹማምንቱም ሬሳውን በሙሉ ወደ ውጭ አውጥተው ጣሉ። ከዚያም ወደ ውስጠኛው የበኣል ቤተ ጣዖት ገቡ።

26. ከድንጋይ የተሠሩትንም ማምለኪያ ምስሎች ከበኣል ቤተ ጣዖት አውጥተው አቃጠሉ።

27. የበኣልን ማምለኪያ ምስል ቀጠቀጡ፤ የበኣልንም ቤተ አምልኮ አፈረሱ፤ ይህንንም ሕዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ የኵስ መጣያው አድርጎታል።

28. በዚህ ሁኔታም ኢዩ የበኣልን አምልኮ ከእስራኤል አስወገደ።

29. ይሁን እንጂ ኢዩ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ በቤቴልና በዳን የወርቅ ጥጃዎች እንዲያመልኩ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀም።

30. እግዚአብሔርም ኢዩን፣ “በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር ስላደረግህና በአክዓብም ቤት ላይ እንዲደርስ በልቤ ያለውን ሁሉ ስለፈጸምህ፤ ዘርህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣል” አለው።

31. ነገር ግን ኢዩ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ልቡ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀምና።

32. በዚያ ዘመን እግዚአብሔር የእስራኤልን ምድር መቀናነስ ጀመረ። አዛሄልም እስራኤልን ዳር እስከ ዳር መታ።

2 ነገሥት 10