2 ነገሥት 10:23-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ከዚያም ኢዩ ከሬካብ ልጅ ከኢዮናዳብ ጋር ወደ በኣል ቤተ ጣዖት ገባ። የበኣልንም አገልጋዮች፣ “እንግዲህ የበኣል አገልጋዮች ብቻ እንጂ የእግዚአብሔር አገልጋዮች እዚህ አብረዋችሁ አለመኖራቸውን አረጋግጡ” አላቸው።

24. ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላም መሥዋዕት ለማቅረብ ገቡ። በዚህ ጊዜም ኢዩ፣ “በእጃችሁ አሳልፌ ከሰጠኋችሁ ሰዎች አንድ እንኳ እንዲያመልጥ ያደረገ በገመዱ ይገባበታል” ብሎ በማስጠንቀቅ ውጭ ሰማንያ ሰዎች አዘጋጅቶ ነበር።

25. ኢዩ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርቦ እንዳበቃ ጠባቂዎቹንና የጦር አለቆቹን፣ “ግቡና ግደሏቸው፤ ማንም እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ። እነርሱም በሰይፍ ፈጇቸው፤ ጠባቂዎቹና የጦር ሹማምንቱም ሬሳውን በሙሉ ወደ ውጭ አውጥተው ጣሉ። ከዚያም ወደ ውስጠኛው የበኣል ቤተ ጣዖት ገቡ።

26. ከድንጋይ የተሠሩትንም ማምለኪያ ምስሎች ከበኣል ቤተ ጣዖት አውጥተው አቃጠሉ።

27. የበኣልን ማምለኪያ ምስል ቀጠቀጡ፤ የበኣልንም ቤተ አምልኮ አፈረሱ፤ ይህንንም ሕዝቡ እስከ ዛሬ ድረስ የኵስ መጣያው አድርጎታል።

28. በዚህ ሁኔታም ኢዩ የበኣልን አምልኮ ከእስራኤል አስወገደ።

29. ይሁን እንጂ ኢዩ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም፣ በቤቴልና በዳን የወርቅ ጥጃዎች እንዲያመልኩ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀም።

30. እግዚአብሔርም ኢዩን፣ “በፊቴ መልካም የሆነውን ነገር ስላደረግህና በአክዓብም ቤት ላይ እንዲደርስ በልቤ ያለውን ሁሉ ስለፈጸምህ፤ ዘርህ እስከ አራት ትውልድ ድረስ በእስራኤል ዙፋን ላይ ይቀመጣል” አለው።

31. ነገር ግን ኢዩ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በፍጹም ልቡ ለመጠበቅ ጥንቃቄ አላደረገም፤ ኢዮርብዓም፣ እስራኤልን ካሳተበት ኀጢአት አልራቀምና።

2 ነገሥት 10