2 ነገሥት 1:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. ስለዚህም ንጉሡ ሦስተኛውን የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎቹ ጋር ላከ። ይህም ሦስተኛው የአምሳ አለቃ ወጥቶ፣ በኤልያስ ፊት በጒልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ እባክህ የእኔና የእነዚህ የአምሳዎቹ አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን።

14. እነሆ፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ የፊተኞቹን ሁለት አምሳ አለቆችና ሰዎቻቸውን ሁሉ በላች፤ አሁን ግን ሕይወቴ በፊትህ የከበረች ትሁን።”

15. የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን፣ “አብረኸው ውረድ፤ ደግሞም አትፍራው” አለው። ስለዚህ ኤልያስ ተነሣ፤ አብሮትም ወደ ንጉሡ ወረደ።

16. ንጉሡንም፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ለመሆኑ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ስለ ራስህ ለመጠየቅ መልእክተኞች የላክኸው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን? ይህን በማድረግህም ከተኛህበት ዐልጋ ፈጽሞ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ’ ” ብሎ ነገረው።

17. ስለዚህ አካዝያስ ኤልያስ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሞተ።አካዝያስ ወንድ ልጅ ስላልነበረው፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም በይሁዳ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ወንድሙ ኢዮራም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

18. ሌላው አካዝያስ በዘመኑ ያከናወናቸውና የፈጸማቸው ሥራዎች ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ የተጻፉ አይደለምን?

2 ነገሥት 1