2 ተሰሎንቄ 3:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. የእኛን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደሚገባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና። ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤

8. ደግሞም የማንንም እንጀራ በነጻ አልበላንም፤ ነገር ግን ከእናንተ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እንደክምና እንሠራ ነበር፤

9. ይህን ያደረግነው ምሳሌነታችንን እንድትከተሉ ብለን እንጂ የሚያስፈልገንን ነገር ከእናንተ ለማግኘት ሥልጣን ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም።

10. ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ፣ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ብለን ይህን ትእዛዝ ሰጥተናችሁ ነበርና።

11. ከእናንተ አንዳንዶች ሥራ ፈቶች እንደሆኑ ሰምተናል፤ እነርሱም ያለ ሥራ እየዞሩ በሰው ጒዳይ ጣልቃ የሚገቡ ናቸው።

12. እንደዚህ ያሉ ሰዎች ተግተው ሥራቸውን እንዲሠሩና እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም።

13. እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ፤ መልካም ሥራን ከመሥራት ከቶ አትታክቱ።

2 ተሰሎንቄ 3