2 ቆሮንቶስ 7:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እንግዲህ፣ ወዳጆች ሆይ፤ ይህ የተስፋ ቃል ስላለን፣ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርገው።

2. ልባችሁን አስፉልን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም ወደ ብልሹነት አልመራንም፤ ማንንም አላታለልንም።

3. ይህን የምለው ልኰንናችሁ አይደለም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርኋችሁ፣ በልባችን ውስጥ ስፍራ አላችሁ፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም አብረን ነው።

4. በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ትልቅ ነው፤ በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም።

5. ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን።

6. ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን።

7. የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል።

2 ቆሮንቶስ 7