1. መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን።
2. እስከዚያው ግን የሰማዩን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን እንቃትታለን፤
3. በርግጥ ከለበስነው ራቊታችንን ሆነን አንገኝም።
4. በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም።
5. ለዚህ ዐላማ ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ሊመጣ ላለው ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን መያዣ አድርጎ የሰጠንም እርሱ ነው።