2 ቆሮንቶስ 12:6-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. መመካት ብፈልግ እንኳ እንደ ሞኝ መቈጠር የለብኝም፤ ምክንያቱም የምናገረው እውነት ነው። ነገር ግን ማንም ስለ እኔ ከሚያየውና ከሚሰማው በላይ እንዳይገምተኝ ከመመካት እቈጠባለሁ።

7. ከዚህ ታላቅ መገለጥ የተነሣ እንዳልታ በይ የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ።

8. ይህ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ፣ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት፤

9. እርሱ ግን፣ “ጸጋዬ ይበቃሃል፤ ኀይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነውና” አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኀይል በእኔ ያድር ዘንድ፣ ይበልጥ ደስ እያለኝ በድካሜ እመካለሁ።

10. ስለ ክርስቶስ በድካም፣ በስድብ፣ በመከራ፣ በስደትና በጭንቀት ደስ የምሰኘው ለዚህ ነው፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።

11. በመመካቴ ሞኝ ሆኛለሁ፤ ለዚህም ያበቃችሁኝ እናንተ ናችሁ፤ ስለ እኔ መመስከር የሚገባችሁ እናንተ ነበራችሁ። ደግሞም እኔ ከምንም የማልቈጠር ብሆንም፣ “ታላላቅ ሐዋርያት” ከሚባሉት በምንም አላንስም።

12. የእውነተኛ ሐዋርያ ምልክቶች በመካከላችሁ ተደርገዋል፤ እነርሱም በትዕግሥት መጽናት፣ ምልክቶች፣ ድንቅ ነገሮችና ታምራት ናቸው።

13. በእናንተ ላይ ሸክም ካለመሆኔ በቀር፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በምን አነሳችሁ? ይህን በደሌን ይቅር በሉኝ።

14. ወደ እናንተ ለመምጣት ስዘጋጅ ይህ ሦስተኛዬ ነው፤ ስመጣ በምንም ነገር ሸክም አልሆንባችሁም፤ እኔ እናንተን እንጂ ከእናንተ ምንም አልፈልግምና፤ ደግሞም ወላጆች ለልጆች ገንዘብ ያከማቻሉ እንጂ ልጆች ለወላጆች አያከማቹም።

15. እኔ ግን ስለ እናንተ ያለኝን ሁሉ ራሴንም ጭምር ብሰጥ ደስ ይለኛል፤ ታዲያ እኔ የምወዳችሁ ይህን ያህል ከሆነ፣ እናንተ የምትወዱኝ በጥቂቱ ነውን?

16. የሆነው ሆኖ ሸክም አልሆንሁባችሁም፤ ነገር ግን በተንኰልና በዘዴ ያጠመድኋችሁ ሳይመስላችሁ አልቀረ

17. ለመሆኑ ወደ እናንተ በላክኋቸው ሰዎች አማካይነት በአንዱ እንኳ በዘበዝኋችሁን?

2 ቆሮንቶስ 12