16. ቤትህና መንግሥትህ በፊቴ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤ ዙፋንህም እንደዚሁ ለዘላለም የጸና ይሆናል።’ ”
17. ናታንም የዚህን የጠቅላላውን ራእይ ቃል በሙሉ፣ ለዳዊት ነገረው።
18. ከዚያም ንጉሥ ዳዊት ገባ፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀምጦ እንዲህ አለ፤“ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እስከዚህ ያደረስኸኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድን ነው?
19. ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ በፊትህ ጥቂት ሆኖ ሳለ፤ አንተ ግን ስለ ወደፊቱ የባሪያህ ቤት ተናገርህ፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ከሰው ጋር የምታደርገው ግንኙነት ለካ እንዲህ ነው?
20. “ዳዊት ከዚህ በላይ ምን ሊልህ ይችላል? ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህን አንተ ታውቀዋለህና!
21. ስለ ቃልህና እንደ ልብህ ሐሳብ ይህን ታላቅ ነገር አድርገሃል፤ ባሪያህም እንዲያውቀው ገልጸህለታል።
22. ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! ከቶ የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሮአችን እንደ ሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም።