1. ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ተደላድሎ ከተቀመጠና እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ካሳረፈው በኋላ፣
2. ነቢዩን ናታንን፣ “እነሆ፤ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤተ መንግሥት ውስጥ እኖራለሁ፤ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በድንኳን ውስጥ ይኖራል” አለው።
3. ናታንም፣ “እግዚአብሔር ካንተ ጋር ስለ ሆነ፣ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ” አለው።
4. በዚያች ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ናታን መጣ፤
5. “ሂድና ባሪያዬን ዳዊትን፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የምኖርበትን ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤
6. እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ድንኳንን ማደሪያዬ አድርጌ ከቦታ ወደ ቦታ ተጓዝሁ እንጂ በቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም።