2 ሳሙኤል 19:25-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

25. እርሱም ንጉሡን ለመቀበል ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሜምፊቦስቴ፣ አብረኸኝ ያልሄድኸው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

26. እርሱም እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ ሽባ በመሆኔ፣ ‘ከንጉሡ ጋር መሄድ እንድችል አህያዬ ይጫንልኝና ልቀመጥበት’ ብዬ ነበር፤ ይሁን እንጂ አገልጋዬ ሲባ አታለለኝ።

27. በጌታዬ በንጉሡ ፊትም የእኔን የባሪያህን ስም አጥፍቶአል፤ መቼም ንጉሥ ጌታዬ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንህ ደስ ያለህን ሁሉ አድርግ።

28. የአባቴ ቤት ሁሉ ከንጉሥ ጌታዬ ሞት እንጂ ሌላ የሚገባው አልነበረም፤ አንተ ግን ባሪያህን በማእድህ ከሚካፈሉት ጋር አስቀመጥኸው፤ ከዚህ በላይ ይደረግልኝ ብዬ ንጉሡን ለመጠየቅ ምን መብት አለኝ?”

29. ንጉሡም፣ “ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ ዕርሻውን ሁሉ እንድትካፈሉ አዝዣለሁ” አለው።

30. ሜምፊቦስቴም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ጌታዬ እንኳን በደኅና ተመለሰ እንጂ፣ እርሱ ሁሉንም ይውሰደው” አለው።

31. እንዲሁም ገለዓዳዊው ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፤ ንጉሡን ለመሸኘትም አብሮት ዮርዳኖስን ተሻገረ።

32. በዚያን ጊዜ ቤርዜሊ በዕድሜ የገፋ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበር፤ እጅግ ባለጸጋ ስለ ነበረም ንጉሡ በመሃናይም ሳለ የሚመገበውን አምጥቶለት ነበር።

33. ንጉሡም ቤርዜሊን፣ “ከእኔ ጋር ተሻገርና በኢየሩሳሌም አብረኸኝ ኑር፤ እኔ እመግብሃለሁ” አለው።

34. ቤርዜሊ ግን ለንጉሡ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የምሄደው ለየትኛው ዕድሜዬ ብዬ ነው?

35. እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፤ ታዲያ ደግና ክፉውን መለየት እችላለሁ? ከእንግዲህ አገልጋይህ የሚበላውንና የሚጠጣውን ጣዕሙን መለየት ይችላል? የሚዘፍኑትን የወንዶችና የሴቶችን ድምፅ አሁንም መስማት እችላለሁ? ታዲያ አገልጋይህ ለንጉሥ ጌታዬ ለምን ተጨማሪ ሸክም ይሆናል?

36. አገልጋይህ ዮርዳኖስን ተሻግሮ ከንጉሡ ጋር ጥቂት መንገድ ይሄዳል፤ ነገር ግን ንጉሡ በዚህ ሁኔታ ወሮታ የሚመልስልኝ ለምንድን ነው?

37. በገዛ ከተማዬ ሞቼ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ እቀበር ዘንድ፣ አገልጋይህን አሰናብተውና ይመለስ፤ ነገር ግን አገልጋይህ ከመዓም እነሆ፤ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይሻገር፤ ደስ ያለህንም ነገር አድርግለት።”

38. ንጉሡም፣ “ከመዓም ከእኔ ጋር ይሻገራል፤ አንተን ደስ የሚያሰኝህንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ከእኔ የምትፈልገውን ማናቸውንም ነገር ለአንተም አደርግልሃለሁ” አለው።

39. ስለዚህም ሕዝቡ በሙሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ከዚያ በኋላም ንጉሡ ተሻገረ። ንጉሡ ቤርዜሊን ስሞ መረቀው፤ ቤርዜሊም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

2 ሳሙኤል 19