2 ሳሙኤል 15:8-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. እኔ አገልጋይህ በሶርያ ምድር በጌሹር ሳለሁ ‘እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም የመለሰኝ እንደሆነ፣ በኬብሮን ለእግዚአብሔር እሰግዳለሁ’ ብዬ ተስያለሁ።”

9. ንጉሡም፣ “በሰላም ሂድ” አለው፤ ስለዚህ አቤሴሎም ወደ ኬብሮን ሄደ።

10. ከዚያም አቤሴሎም፣ “የቀንደ መለከት ድምፅ ስትሰሙ፣ ‘አቤሴሎም በኬብሮን ነገሠ በሉ” የሚሉ የምስጢር ሠራተኞችን በመላው የእስራኤል ነገዶች አሰማራ።

11. ከኢየሩሳሌምም ሁለት መቶ ሰዎች አብረውት ሄዱ፤ በእንግድነት ተጋብዘው በየዋህነት ከመሄዳቸው በስተቀር፣ ስለ ጒዳዩ የሚያውቁት አንዳችም ነገር አልነበረም።

12. አቤሴሎም መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የዳዊት አማካሪ የሆነው ጊሎአዊው አኪጦፌል ከአገሩ ከጊሎ ወደ እርሱ እንዲመጣ ላከበት፤ ስለዚህ ሤራው ጥንካሬ አገኘ፤ የአቤሴሎምም ተከታዮች ቍጥር እየጨመረ መጣ።

13. መልእክተኛም መጥቶ፣ “የእስራኤል ሰዎች ልብ ከአቤሴሎም ጋር ሆኖአል” ብሎ ለዳዊት ነገረው።

14. ከዚያም ዳዊት በኢየሩሳሌም ላሉት ሹማምቱ ሁሉ፣ “ተነሡ እንሽሽ፤ ያለበለዚያ አንዳችንም ከአቤሴሎም እጅ ማምለጥ አንችልም፤ አሁኑኑ ከዚህ መውጣት አለብን፤ ካልሆነ ገሥግሦ መጥቶ ከያዘን እኛን ያጠፋናል፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ይመታታል” አላቸው።

15. የንጉሡ ሹማምትም፣ “ጌታችን ንጉሡ የመረጠውን ሁሉ ለማድረግ እኛ አገልጋዮችህ ዝግጁ ነን” ብለው መለሱለት።

16. ንጉሡ ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር ወጣ፤ ቤተ መንግሥቱንም እንዲጠብቁ ዐሥር ቁባቶች አስቀረ።

17. ስለዚህ ንጉሡ መላውን ሕዝብ አስከትሎ ወጣ፤ ጥቂት ርቀው ከሄዱ በኋላም በአንዲት ቦታ ቆሙ።

18. ሰዎቹ ሁሉ፣ ከሊታውያን፣ ፈሊታውያን እንዲሁም ከጌት አብረውት የመጡትን ስድስት መቶ ጌታውያንን ሁሉ ጨምሮ ተሰልፈው በንጉሡ ፊት ዐለፉ።

19. ንጉሡም ጌታዊውን ኢታይን እንዲህ አለው፤ “ከእኛ ጋር የመጣኸው ለምንድን ነው? ተመለስና ከንጉሡ ከአቤሴሎም ጋር ተቀመጥ፤ አንተ ለራስህ ከአገርህ ተወስደህ የመጣህ እንግዳ ነህ፤

20. የመጣኸውም ገና ትናንት ነው፤ ታዲያ የት እንደምሄድ የማላውቅ ሰው እንዴት ዛሬ ከእኛ ጋር እንድትንከራተት ላድርግ? በል አሁንም ሰዎችህን ይዘህ ተመለስ፤ በጎነትና ታማኝነትም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው።

2 ሳሙኤል 15