1. የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ።
2. ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ፤ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት መስለሽም ታዪ።
3. ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እንዲህ በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ የምትናገራቸውን ቃላት ነገራት።
4. የቴቁሔዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፣ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት በግምባሯ ተደፍታ እጅ በመንሣት አክብሮቷን ከገለጠች በኋላ፣ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች።
5. ንጉሡም፣ “ችግርሽ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃት።እርሷም እንዲህ አለች፤ “እኔ በእርግጥ ባሌ የሞተብኝ መበለት ነኝ፤
6. እኔ አገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ ሜዳ ላይ እርስ በርሳቸው ተጣሉ፤ ገላጋይም ስላልነበረ፣ አንዱ ሌላውን መትቶ ገደለው።