1. “ማንም ኤጲስቆጶስነትን ቢፈልግ፣ መልካም ሥራን ይመኛል” የሚለው ቃል የታመነ ነው።
2. እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ኤጲስቆጶስ የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልከኛ፣ ራሱን የሚገዛ፣ በሥርዐት የሚኖር፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ማስተማር የሚችል፣
3. የማይሰክር፣ የማይጣላ ግን ጨዋ የሆነ፣ የማይጨቃጨቅ፣ ገንዘብንም የማይወድ ሊሆን ይገባዋል።
4. ልጆቹን ታዛዥና አክባሪ አድርጎ በማሳደግ የገዛ ቤተ ሰቡን በአግባቡ የሚያስተዳድር ሊሆን ይገባል።
5. አንድ ሰው የራሱን ቤት ማስተዳደር ካላወቀበት፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ሊጠብቅ ይችላል?
6. በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ በወደቀበት ፍርድ እንዳይወድቅ አዲስ ክርስቲያን አይሁን።
7. ደግሞም ስሙ እንዳይነቀፍና በዲያብሎስ ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ፣ በውጭ ባሉት ዘንድ መልካም ምስክርነት ሊኖረው ይገባል።
8. ዲያቆናትም እንደዚሁ የተከበሩ፣ ቃላቸውን የማይለዋውጡ፣ ለብዙ ወይን ጠጅ የማይጐመጁ፣ ያለ አግባብ የሚገኝ ጥቅምንም የማያሳድዱ ሰዎች መሆን ይገባቸዋል፤