8. በሌላ በኩል የምጽፍላችሁ ጨለማው ዕያለፈና እውነተኛው ብርሃን እየበራ ስለ ሆነ፣ በእርሱም፣ በእናንተም ዘንድ እውነት የሆነውን አዲስ ትእዛዝ ነው።
9. በብርሃን አለሁ የሚል፣ ወንድሙን ግን የሚጠላ አሁንም በጨለማ ውስጥ አለ።
10. ወንድሙን የሚወድ በብርሃን ይኖራል፤ በእርሱም ዘንድ የመሰናከያ ምክንያት የለውም።
11. ነገር ግን ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ውስጥ ነው፤ በጨለማ ይመላለሳል፤ ጨለማው ስላሳወረውም የት እንደሚሄድ አያውቅም።
12. ልጆች ሆይ፤ኀጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና፣እጽፍላችኋለሁ።
13. አባቶች ሆይ፤ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።ጐበዛዝት ሆይ፤ ክፉውን አሸንፋችኋልና፣ እጽፍላችኋለሁ።ልጆች ሆይ፤ አብን ዐውቃችሁታልና፣ እጽፍላችኋለሁ።
14. አባቶች ሆይ፤ከመጀመሪያ ያለውን እርሱን ዐውቃችሁታልና፣እጽፍላችኋለሁ።ጐበዛዝት ሆይ፤ብርቱዎች ስለ ሆናችሁ፣የእግዚአብሔር ቃል በእናንተ ስለሚኖር፣ክፉውንም ስላሸነፋችሁ፣ጽፍላችኋለሁ።
15. ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤
16. ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም።
17. ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።
18. ልጆች ሆይ፤ ይህ የመጨረሻው ሰዓት ነው፤ እንደሰማችሁትም የክርስቶስ ተቃዋሚ ይመጣል፤ አሁን እንኳ ብዙ የክርስቶስ ተቃዋሚዎች መጥተዋል፤ የመጨረሻው ሰዓት እንደሆነ የምናውቀውም በዚህ ነው።
19. ከእኛ መካከል ወጡ፤ ይሁን እንጂ ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገን ቢሆኑማ ኖሮ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር። ነገር ግን ሁሉም ከእኛ ወገን እንዳልነበሩ ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ተለዩ።