1 ዜና መዋዕል 26:20-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

20. ከሌዋውያን መካከል አኪያ የእግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤትና የተቀደሱት ዕቃዎች የሚቀመጡበት ግምጃ ቤት ኀላፊ ነበረ።

21. የለአዳን ዘሮች፣ በለኣዳን በኩል ጌድሶናውያን የሆኑትና ለጌድሶናዊው ለለአዳን ቤተ ሰቦች አለቆች የሆኑት የለአዳን ዘሮች እነዚህ ነበሩ፤ ይሒኤሊ፣

22. የይሒኤሊ ወንዶች ልጆች፣ ዜቶምና ወንድሙ ኢዩኤል። እነዚህም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ነበሩ።

23. ከእንበረማውያን፣ ከይስዓራውያን፣ ከኬብሮናውያን፣ ከዑዝኤላውያን፤

24. የሙሴ ልጅ የጌርሳም ዘር የሆነው ሱባኤል የግምጃ ቤቱ የበላይ ኀላፊ ነበረ።

25. በአልዓዛር በኩል የሚዛመዱት፤ ልጁ ረዓብያ፣ ልጁ የሻያ፣ ልጁ ኢዮራም፣ ልጁ ዝክሪ፣ ልጁ ሰሎሚት።

26. ሰሎሚትና የሥጋ ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት፣ የቤተ ሰቡ ኀላፊዎች፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ አዛዦች ቀድሰው ላቀረቧቸው ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ።

27. በጦርነት ከተገኘውም ምርኮ ከፊሉን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማደሻ እንዲሆን ቀደሱት።

28. ባለ ራእዩ ሳሙኤል፣ የቂስ ልጅ ሳኦል፣ የኔር ልጅ አበኔር፣ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የቀደሱትን ሁሉና እንዲሁም ሌሎቹን ንዋያተ ቅድሳት ሰሎሚናትና ቤተ ዘመዶቹ ይጠብቁ ነበር።

1 ዜና መዋዕል 26