1 ዜና መዋዕል 26:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ሁለተኛው ኬልቅያስ፣ ሦስተኛው ጥበልያ፣ አራተኛው ዘካርያስ፤ የሖሳ ወንዶች ልጆችና ቤተ ዘመዶቹ ባጠቃላይ ዐሥራ ሦስት ነበሩ።

12. የቤተ መቅደሱም ጠባቂዎች በአለቆቻቸው ሥር ተመድበው ልክ እንደ ቤተ ዘመዶቻቸው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ ለማከናወን ምድብ ተራ ነበራቸው።

13. ለእያንዳንዱም በር ወጣት ሽማግሌ ሳይባል ለሁሉም እኩል ዕጣ ተጣለ።

14. የምሥራቁ በር ዕጣ ለሴሌምያ ወጣ። ከዚያም ምክር ዐዋቂ ለሆነው ለልጁ ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ እርሱም የሰሜኑ በር ደረሰው።

15. የደቡቡ በር ዕጣ ለዖቤድኤዶም ሲወጣ፣ የግምጃ ቤቱ ዕጣ ደግሞ ለልጆቹ ወጣ።

16. የምዕራቡ በርና በላይኛው መንገድ ላይ የሚገኘው የሸሌኬት በር ዕጣዎች ለሰፊንና ለሖሳ ወጣ።

17. በአንዱ ዘብ ጥበቃ ትይዩ ሌላ ዘብ ጥበቃ ነበረ፤ በየቀኑም በምሥራቅ በኩል ስድስት፣ በሰሜን በኩል አራት፣ በደቡብ በኩል አራት፣ በዕቃ ቤቱ በኩል በአንድ ጊዜ ሁለት ሌዋውያን ይጠብቁ ነበር።

18. በምዕራቡ በኩል የሚገኘውን አደባባይ ደግሞ በመንገዱ ላይ አራት፣ በአደባባዩ ላይ ደግሞ ሁለት ሆነው ይጠብቁ ነበር።

19. እንግዲህ የቆሬና የሜራሪ ዘሮች የሆኑት በር ጠባቂዎች ድልድል ይህ ነበር።

20. ከሌዋውያን መካከል አኪያ የእግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤትና የተቀደሱት ዕቃዎች የሚቀመጡበት ግምጃ ቤት ኀላፊ ነበረ።

21. የለአዳን ዘሮች፣ በለኣዳን በኩል ጌድሶናውያን የሆኑትና ለጌድሶናዊው ለለአዳን ቤተ ሰቦች አለቆች የሆኑት የለአዳን ዘሮች እነዚህ ነበሩ፤ ይሒኤሊ፣

22. የይሒኤሊ ወንዶች ልጆች፣ ዜቶምና ወንድሙ ኢዩኤል። እነዚህም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት ኀላፊዎች ነበሩ።

23. ከእንበረማውያን፣ ከይስዓራውያን፣ ከኬብሮናውያን፣ ከዑዝኤላውያን፤

24. የሙሴ ልጅ የጌርሳም ዘር የሆነው ሱባኤል የግምጃ ቤቱ የበላይ ኀላፊ ነበረ።

25. በአልዓዛር በኩል የሚዛመዱት፤ ልጁ ረዓብያ፣ ልጁ የሻያ፣ ልጁ ኢዮራም፣ ልጁ ዝክሪ፣ ልጁ ሰሎሚት።

26. ሰሎሚትና የሥጋ ዘመዶቹ ንጉሥ ዳዊት፣ የቤተ ሰቡ ኀላፊዎች፣ የሻለቆችና የመቶ አለቆች እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ አዛዦች ቀድሰው ላቀረቧቸው ንዋያተ ቅድሳት ኀላፊዎች ነበሩ።

27. በጦርነት ከተገኘውም ምርኮ ከፊሉን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ማደሻ እንዲሆን ቀደሱት።

1 ዜና መዋዕል 26