1 ዜና መዋዕል 16:12-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤

13. እናንተ የባሪያው የእስራኤል ዘሮች፣እናንተ የተመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች።

14. እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው፤

15. ኪዳኑን እስከ ዘላለም፣ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺህ ትውልድ ያስባል።

16. ከአብርሃም ጋር የገባውን ቃል ኪዳን፣ለይስሐቅ የማለውን መሐላ።

17. ይህንንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ አጸና፤ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አደረገ፤

18. እንዲህ ሲል፣ “የምትወርሰው ርስት እንዲሆን፣የከነዓንን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ።”

19. ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣በእርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣

20. ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው መንግሥት ተንከራተቱ።

21. ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤

22. እንዲህ ሲል፤ “የቀባኋቸውን አትንኩ፤በነቢያቴ ላይ ክፉ አታድርጉ።

23. ምድር ሁሉ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ማዳኑንም ዕለት ዕለት ዐውጁ።

24. ክብሩን ለአሕዛብ ተናገሩ፤ድንቅ ሥራዎቹን ለሕዝቦች ሁሉ ንገሩ።

25. እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምስጋናውም ብዙ ነው፤ከአማልክትም ሁሉ በላይ ሊፈራ የሚገባው ነው።

26. የአሕዛብ ሁሉ አማልክት ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።

27. በፊቱ ክብርና ሞገስ አለ፤ብርታትና ደስታም በማደሪያው ስፍራ።

28. የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር ስጡ፤ክብርና ኀይልን ለእግዚአብሔር አምጡ።

29. ለስሙ የሚገባውን ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤መባ ይዛችሁ በፊቱ ቅረቡ፤በቅድስናውም ክብር ለእግዚአብሔር ስገዱ።

30. ምድር ሁሉ በፊቱ ትንቀጥቀጥ፤ዓለም በጽኑ ተመሥርታለች፤ አትናወጥምም።

31. ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ ምድር ሐሤት ታድርግ፤በአሕዛብም መካከል፤ “እግዚአብሔር ነገሠ!” ይበሉ።

32. ባሕርና በውስጧ ያለው ሁሉ ይናወጥ፤ሜዳዎችና በእርሷ ላይ ያሉ ሁሉ ሐሤት ያድርጉ።

1 ዜና መዋዕል 16