20. ዳዊት ወደ ጺቅላግ በሄደ ጊዜ ከድተው ወደ እርሱ የተቀላቀሉ የምናሴ ነገድ ሰዎች እነዚህ ነበሩ፤ ዓድና፣ ዮዛባት፣ ይዲኤል፣ ሚካኤል፣ ዮዛባት፣ ኤሊሁ፣ ጺልታይ፤ እነዚህ በምናሴ ግዛት ሳሉ የሻለቆች ነበሩ።
21. ሁሉም ብርቱ ተዋጊዎችና በዳዊትም ሰራዊት ውስጥ አዛዦች ስለ ነበሩ፣ አደጋ ጣዮችን በመውጋት ረዱት።
22. ሰራዊቱም እንደ እግዚአብሔር ሰራዊት እስኪሆን ድረስ፣ ዳዊትን ለመርዳት በየዕለቱ ብዙ ሰዎች ይጎርፉ ነበር።
23. እግዚአብሔር ለዳዊት በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት የሳኦልን መንግሥት አንሥተው ለእርሱ ለመስጠት ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ ኬብሮን የመጡት ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤
24. ጋሻና ጦር አንግበው ለጦርነት የተዘጋጁት የይሁዳ ሰዎች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ፤
25. ከስምዖን ነገድ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ሰባት ሺህ አንድ መቶ።
26. ከሌዊ ነገድ አራት ሺህ ስድስት መቶ፤
27. የአሮን ቤተ ሰብ መሪ የሆነውን ዮዳሄን ጨምሮ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፤
28. ወጣቱ ብርቱ ተዋጊ ጻዶቅና ከቤተ ሰቡ ሃያ ሁለት የጦር አለቆች፤
29. የሳኦል ሥጋ ዘመድ የሆኑ የብንያም ሰዎች ሦስት ሺህ፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለሳኦል ቤት ታማኝ ነበሩ፤
30. ከኤፍሬም ሰዎች በጐሣዎቻቸው ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ብርቱ ተዋጊዎች ሃያ ሺህ ስምንት መቶ፤
31. ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች፤ እነርሱም ዳዊትን ለማንገሥ በየስማቸው ተጽፈው የመጡ ነበሩ።