1 ዜና መዋዕል 12:17-34 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ዳዊትም እነዚህን ሰዎች ሊቀበል ወጥቶ እንዲህ አላቸው፤ የመጣችሁት ልትረዱኝና በሰላም ከሆነ፣ ከእኔ ጋር እንድትሰለፉ ልቀበላችሁ ዝግጁ ነኝ፤ ነገር ግን እጄ ከበደል ንጹሕ ሆኖ ሳለ፣ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ ከሆነ፣ የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፤ ይፍረደውም”።

18. ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በሠላሳዎቹ አለቃ በዓማሣይ ላይ ወረደ፤ እርሱም እንዲህ አለ፤“ዳዊት ሆይ፤ እኛ የአንተ ነን፤የእሴይ ልጅ ሆይ፤ እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ሰላም ፍጹም ሰላም ለአንተ ይሁን፤አንተን ለሚረዱም ሁሉ ሰላም ይሁን፤አምላክህ ይረዳሃልና”።ስለዚህ ዳዊት ተቀበላቸው፤ የሰራዊቱም አለቃ አደረጋቸው።

19. ዳዊት ከፍልስጥኤማውያን ጋር ተባብሮ ሳኦልን ለመውጋት በሄደ ጊዜ፣ ከምናሴ ነገድ የሆኑ ጥቂት ሰዎች ከድተው ከዳዊት ሰራዊት ጋር ተቀላቀሉ። እርሱ ግን ርዳታ አላደረገላቸውም፤ ምክንያቱም የፍልስጥኤማውያን ገዦች ምክር ካደረጉ በኋላ እንዲህ ሲሉ ልከውት ነበር፤ “ከድቶ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ቢሄድ እኛን ያስጨርሰናል”።

20. ዳዊት ወደ ጺቅላግ በሄደ ጊዜ ከድተው ወደ እርሱ የተቀላቀሉ የምናሴ ነገድ ሰዎች እነዚህ ነበሩ፤ ዓድና፣ ዮዛባት፣ ይዲኤል፣ ሚካኤል፣ ዮዛባት፣ ኤሊሁ፣ ጺልታይ፤ እነዚህ በምናሴ ግዛት ሳሉ የሻለቆች ነበሩ።

21. ሁሉም ብርቱ ተዋጊዎችና በዳዊትም ሰራዊት ውስጥ አዛዦች ስለ ነበሩ፣ አደጋ ጣዮችን በመውጋት ረዱት።

22. ሰራዊቱም እንደ እግዚአብሔር ሰራዊት እስኪሆን ድረስ፣ ዳዊትን ለመርዳት በየዕለቱ ብዙ ሰዎች ይጎርፉ ነበር።

23. እግዚአብሔር ለዳዊት በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት የሳኦልን መንግሥት አንሥተው ለእርሱ ለመስጠት ዳዊት ወደሚገኝበት ወደ ኬብሮን የመጡት ሰዎች ቍጥር ይህ ነው፤

24. ጋሻና ጦር አንግበው ለጦርነት የተዘጋጁት የይሁዳ ሰዎች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ፤

25. ከስምዖን ነገድ ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ሰባት ሺህ አንድ መቶ።

26. ከሌዊ ነገድ አራት ሺህ ስድስት መቶ፤

27. የአሮን ቤተ ሰብ መሪ የሆነውን ዮዳሄን ጨምሮ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፤

28. ወጣቱ ብርቱ ተዋጊ ጻዶቅና ከቤተ ሰቡ ሃያ ሁለት የጦር አለቆች፤

29. የሳኦል ሥጋ ዘመድ የሆኑ የብንያም ሰዎች ሦስት ሺህ፤ ከእነዚህም አብዛኞቹ እስከዚያች ጊዜ ድረስ ለሳኦል ቤት ታማኝ ነበሩ፤

30. ከኤፍሬም ሰዎች በጐሣዎቻቸው ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ብርቱ ተዋጊዎች ሃያ ሺህ ስምንት መቶ፤

31. ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች፤ እነርሱም ዳዊትን ለማንገሥ በየስማቸው ተጽፈው የመጡ ነበሩ።

32. ዘመኑን የተረዱና እስራኤላውያንም ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የተገነዘቡ የይሳኮር ሰዎች ሁለት መቶ አለቆች፤ በእነርሱም ሥር ሆነው የሚታዘዙ ዘመዶቻቸው።

33. ልምድ ያላቸው፣ በሁሉም ዐይነት መሣሪያ ለመዋጋት የተዘጋጁና ዳዊትን ለመርዳት የመጡት መንታ ልብ የሌላቸው የዛብሎን ሰዎች ሃምሳ ሺህ፤

34. ከንፍታሌም ሰዎች አንድ ሺህ የጦር አለቆች፤ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የያዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ሰዎች፤

1 ዜና መዋዕል 12