1 ነገሥት 6:9-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

9. ቤተ መቅደሱንም በዚሁ ሁኔታ ሠርቶ ጨረሰ፤ ለጣራው ተሸካሚ አደረገለት፤ በዝግባ ሳንቃም ከደነው።

10. በቤተ መቅደሱም ዙሪያ በሙሉ፣ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆነ ክፍሎች ሠራ፤ እነዚህንም ከቤተ መቅደሱ ጋር በዝግባ አግዳሚ ዕንጨቶች አያያዛቸው።

11. የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሰሎሞን መጣ፤

12. “ስለምትሠራው ስለዚህ ቤተ መቅደስ ሥርዐቴን ብትከተል፣ ፍርዴን በተግባር ብትገልጸው፣ ትእዛዛቴን ብትጠብቅና ብትመላለስባቸው ለአባትህ ለዳዊት የሰጠሁትን ተስፋ በአንተ እፈጽመዋለሁ፤

13. በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤን እስራኤልንም አልተወውም።”

14. ስለዚህ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ፈጸመ፤

15. የውስጡን ግድግዳ ከቤተ መቅደሱ ወለል እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ የቤተ መቅደሱንም ወለል የጥድ ሳንቃ አለበሰው።

16. በቤተ መቅደሱም ውስጥ በስተ ኋላ በኩል፣ ሃያውን ክንድ ቅድስተ ቅዱሳን እንዲሆን፣ ከወለሉ አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ ሳንቃዎች ጋረደው፤

17. በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ያለው ዋና አዳራሽ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበር።

18. የቤተ መቅደሱም፣ ውስጡ በሙሉ በዝግባ የተለበጠ ሲሆን፣ ይህም በእንቡጥ አበቦችና በፈኩ አበቦች ቅርጽ የተጌጠ ነበር፤ በሙሉ ዝግባ እንጂ የሚታይ ድንጋይ አልነበረም።

1 ነገሥት 6