9. ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ፣ “በል የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው።
10. የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር አጠገብ ባለው አውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው ሳለ፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።
11. በዚህ ጊዜ ሴዴቅያስ የተባለው የክንዓና ልጅ የብረት ቀንዶች አበጅቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ የምትወጋቸው በእነዚህ ነው’ ” አለው።
12. የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና በገለዓድ የምትገኘውን ሬማትን ወግተህ ድል አድርግ” በማለት በአንድ ቃል ትንቢት ይናገሩ ነበር።
13. ከዚያም ሚክያስን ሊጠራ የሄደው መልእክተኛ፣ “እነሆ፤ ሌሎቹ ነቢያት ንጉሡ ድል እንደሚያደርግ በአንድ ቃል ትንቢት እየተናገሩለት ነውና ያንተም ቃል ከእነርሱ ጋር አንድ እንዲሆን እባክህ መልካም ነገር ተናገር” አለው።
14. ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ለእርሱ የምነግረው እግዚአብሔር የነገረኝን ብቻ ነው” አለ።