1 ነገሥት 21:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ የወይን ተክል ቦታ ላይ አንድ ነገር ደረሰ፤ ቦታውም በኢይዝራኤል ውስጥ ከሰማርያ ንጉሥ ከአክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ነበር።

2. አክዓብም ናቡቴን፣ “የወይን ተክል ቦታህ ከቤተ መንግሥቴ አጠገብ ስለ ሆነ፣ የአትክልት ቦታ እንዳደርገው ልቀቅልኝ፤ በምትኩ ከዚህ የበለጠ የወይን ተክል ቦታ እሰጥሃለሁ፤ የተሻለ ሆኖ ከታየህም የሚያወጣውን ገንዘብ እከፍልሃለሁ” አለው።

3. ናቡቴ ግን፣ “ዐፅመ ርስቴን እለቅልህ ዘንድ እግዚአብሔር አይበለው” ሲል መለሰለት።

4. ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ፣ “ዐፅመ ርስቴን አልለቅልህም” ስላለው፣ አክዓብ ተበሳጭቶና ተቈጥቶ ወደ ቤቱ ገባ፤ አኵርፎም በዐልጋው ላይ ተኛ፤ ምግብም መብላት ተወ።

5. ሚስቱ ኤልዛቤልም ወደ እርሱ ገብታ፣ “እስከዚህ የተበሳጨኸው፣ ምግብስ የማትበላው ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀችው።

6. እርሱም፣ “ኢይዝራኤላዊውን ናቡቴን፣ ‘የወይን ተክል ቦታህን ሽጥልኝ፤ ከፈለግህም በምትኩ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ’ አልሁት፤ እርሱ ግን፣ ‘የወይን ተክል ቦታዬን አልለቅልህም’ ስላለኝ ነው” አላት።

1 ነገሥት 21