2. ወደ ከተማዪቱም መልእክተኞች በመላክ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን እንዲህ አለው፤ “ቤን ሀዳድ እንዲህ ይላል፤
3. ‘ብርና ወርቅህ የእኔ ነው፤ የሚያማምሩት ሚስቶችህና ልጆችህም የእኔ ናቸው።’ ”
4. የእስራኤልም ንጉሥ፣ “ንጉሥ ጌታዬ ሆይ፤ ልክ እንዳልኸው ነው እኔም ሆንሁ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው” ሲል መለሰለት።
5. መልክተኞቹም እንደ ገና መጥተው እንዲህ አሉት፤ “ቤን ሀዳድ የሚለው ይህ ነው፤ ‘ብርህንና ወርቅህን፣ ሚስቶችህንና ልጆችህን እንድትሰጠኝ ልኬብህ ነበር፤
6. ሆኖም ነገ በዚሁ ጊዜ ቤተ መንግሥትህንና የሹማምትህን ቤቶች እንዲበረብሩ፣ ሹማምቴን እልካቸዋለሁ። እነርሱም ማናቸውንም ለአንተ ዋጋ ያለውን ሁሉ በእጃቸው በማስገባት ይወስዱታል።’ ”
7. የእስራኤልም ንጉሥ የአገሩን ሽማግሌዎች ሁሉ ጠርቶ፣ “ይህ ሰው እንዴት ጠብ እንደሚፈልግ ታያላችሁ ሚስቶቼንና ልጆቼን፣ ብሬንና ወርቄን እንዳስረክበው በጠየቀኝ ጊዜ አልከለከልሁትም” አላቸው።