1 ነገሥት 20:18-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

18. እርሱም፣ “አመጣጣቸው ለሰላምም ይሁን ለጦርነት ከነሕይወታቸው ይዛችሁ አምጧቸው” አለ።

19. የየአውራጃው አዛዥ የሆኑ ወጣት መኰንኖችም ሰራዊቱን አስከትለው ከከተማዪቱ ወጡ፤

20. እያንዳንዱም በፊቱ የገጠመውን ጠላት ገደለ፤ ሶርያውያን ሸሹ፤ እስራኤላውያንም ያሳድዷቸው ጀመር። የሶርያ ንጉሥ ቤን ሀዳድ ግን በፈረሱ ላይ ሆኖ ከጥቂት ፈረሰኞቹ ጋር አመለጠ።

21. የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም ወደ ፊት በመግፋት ፈረሶችንና ሠረገሎችን ማረከ፤ በሶርያውያንም ላይ ከባድ ጒዳት አደረሰባቸው።

22. ከዚያም በኋላ ነቢዩ ወደ እስራኤል ንጉሥ መጥቶ፣ “በሚመጣው የጸደይ ወራት የሶርያ ንጉሥ ተመልሶ ይመጣብሃልና በርታ፤ ምን ማድረግ እንዳለብህም ዕወቅ” አለው።

23. በዚያኑ ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ሹማምት እንዲህ ሲሉ መከሩት፤ “አማልክታቸው የኰረብታ አማልክት ናቸው፤ ያየሉብንም ከዚህ የተነሣ ነው። በሜዳ ላይ ብንገጥማቸው ግን እኛ እንደምናይልባቸው አያጠራጥርም።

24. እንግዲህ እንዲህ አድርግ፤ ነገሥታቱን በሙሉ ከአዛዥነታቸው አስነሣ፤ በቦታቸውም ሌሎች ሹማምት አድርግ።

25. ከእስራኤል ጋር በሜዳው ላይ እንዲጋጠም በፈረሱ ፈንታ ፈረስ፣ በሠረገላው ፈንታ ሠረገላ በመተካት፣ እንደ ተደመሰሰው ያለ ሰራዊት አቋቁም፤ ከዚያ በኋላ ከእነርሱ ይበልጥ እኛ እንደምንበረታ አያጠራጥርም።” ንጉሡም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማማ፤ እንዳሉትም አደረገ።

26. በተከታዩም የጸደይ ወራት ቤን ሀዳድ ሶርያውያንን አሰባስቦ እስራኤልን ለመውጋት ወደ አፌቅ ወጣ።

27. እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው ስንቅ ከተሰጣቸው በኋላ ሊገጥሟቸው ተሰልፈው ወጡ። ሶርያውያን አገር ምድሩን ሞልተውት ሳለ፣ እስራኤላውያን ግን እንደ ሁለት ትናንሽ የፍየል መንጋ ሆነው ከፊት ለፊታቸው ሰፈሩ።

28. የእግዚአብሔርም ሰው ወጥቶ ለእስራኤል ንጉሥ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እግዚአብሔር የኰረብታ እንጂ የሸለቆ አምላክ አይደለም ብለዋልና ይህን ስፍር ቊጥር የሌለው ሰራዊት በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃለህ’ ” አለው።

1 ነገሥት 20