1 ነገሥት 2:30-41 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

30. ስለዚህም በናያስ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው።እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው።በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ።

31. ንጉሡም በናያስን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በል እንዳለው አድርግ፤ ግደልና ቅበረው፤ ኢዮአብ በከንቱ ካፈሰሰው ንጹሕ ደምም እኔንና የአባቴን ቤት አንጻን።

32. አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ በሁለቱ ሰዎች ላይ አደጋ ጥሎ በሰይፍ ገድሎአቸዋልና ስላፈ ሰሰው ደም እግዚአብሔር ይበቀለዋል። የእስራኤል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔርና የይሁዳ ሰራዊት አዛዥ የዬቴሩ ልጅ አሜሳይ ሁለቱም ከእርሱ የተሻሉና ይበልጥ ትክክለኛ ሰዎች ነበሩ።

33. የደማቸውም ዕዳ ለዘላለም በኢዮአብና በዘሩ ራስ ላይ ይሁን። ነገር ግን በዳዊትና በዘሩ፣ በቤቱና በዙፋኑ ላይ የእግዚአብሔር ሰላም ለዘላለም ጸንቶ ይኑር።”

34. ስለዚህም የዮዳሄ ልጅ በናያስ ወጣ፤ ኢዮአብንም መቶ ገደለው፤ እርሱም በምድረ በዳ ባለው በገዛ ምድሩ ተቀበረ።

35. ንጉሡም በኢዮአብ ቦታ የዮዳሄን ልጅ በናያስን በሰራዊቱ ላይ ሾመ፤ በአብያታርም ቦታ ካህኑን ሳዶቅን ተካ።

36. ከዚያም ንጉሡ ሳሚን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ እዚያው ተቀመጥ፤ ከዚያ ግን የትም እንዳትሄድ፤

37. ነገር ግን ከዚያ ወጥተህ የቄድሮንን ሸለቆ ከተሻገርህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።”

38. ሳሚም መልሶ ንጉሡን፣ “መልካም፤ ባሪያህ ጌታዬ ንጉሡ ያለውን ይፈጽማል” አለው፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።

39. ከሦስት ዓመት በኋላ ግን፣ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ፣ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፣ “እነሆ፣ አገልጋዮችህ በጌት ናቸው” ተብሎ ተነገረው።

40. ሳሚ ይህን ሲሰማም አህዮቹን ጭኖ አገልጋዮቹን ለመፈለግ ጌት ወዳለው ወደ አንኩስ ሄደ፤ አገልጋዮቹንም ከጌት መልሶ አመጣቸው።

41. ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ መመለሱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣

1 ነገሥት 2