1 ነገሥት 2:11-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፣ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት ባጠቃላይ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ።

12. ስለዚህ ሰሎሞን በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ የጸና ሆነ።

13. በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ።

14. ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጒዳይ አለኝ” አላት።እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።

15. እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ።

16. አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት።እርሷም፣ “በል እሺ ተናገር” አለችው።

17. እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እምቢ አይልሽምና ሱነማዊቷን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት።

18. ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች።

19. ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጒዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት።

20. እርሷም፣ “የምለምንህ አንዲት ነገር አለችኝና እባክህ እሺ በለኝ” አለችው።ንጉሡም፣ “እናቴ ሆይ፤ አላሳፍርሽምና ንገሪኝ” ሲል መለሰላት።

21. ስለዚህም፣ “ሱነማዊቷን አቢሳን ወንድምህ አዶንያስ ቢያገባትስ?” አለችው።

22. ንጉሥ ሰሎሞንም እናቱን፣ “ስለ ምን ሱነማዊቷን አቢሳን ብቻ ለአዶንያስ ትጠይቂለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ስለ ሆነ መንግሥቱንም ጠይቂለት እንጂ፤ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን እንዲሁም ለካህኑ ለአብያታርና ለጽሩያ ልጅ ለኢዮአብ ጠይቂላቸው” አላት።

23. ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ስም እንዲህ ሲል ማለ፤ “አዶንያስ ይህን ስለ ጠየቀ በሞት ሳይቀጣ ቢቀር፣ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ፤ ከዚህ የባሰም ያምጣብኝ፤

24. አሁንም በሚገባ ያጸናኝ፤ በአባቴ በዳዊት ዙፋን ያስቀመጠኝና በሰጠውም ተስፋ መሠረት ሥርወ መንግሥትን የመሠረተልኝ ሕያው እግዚአብሔርን አዶንያስ ዛሬ ይሞታል!”

25. ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን አዘዘው፤ በናያስም አዶንያስን መቶ ገደለው።

26. ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፣ “ሞት የሚገባህ ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፣ አባቴ የተቀበለውንም መከራ ሁሉ አብረኸው ስለ ተቀበልህ፣ እኔ አሁን አልገድልህም፤ ዓናቶት ወዳለው ዕርሻህ ሂድ” አለው።

27. ስለዚህ እግዚአብሔር ስለ ዔሊ ቤት በሴሎ የተናገረውን ቃል ለመፈጸም፣ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አስወገደው።

28. ከአቤሴሎም ጋር ሳይሆን ከአዶንያስ ጋር አሢሮ የነበረው ኢዮአብም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ።

29. ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መሆኑን ንጉሥ ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፣ የዮዳሄን ልጅ በናያስን፣ “ሂድና ግደለው!” ብሎ አዘዘው።

30. ስለዚህም በናያስ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ገብቶ ኢዮአብን፣ “ንጉሡ፣ ‘ከዚህ ውጣ’ ይልሃል” አለው።እርሱ ግን “አልወጣም፣ እዚሁ እሞታለሁ” አለው።በናያስም፣ “ኢዮአብ የሰጠኝ መልስ ይህ ነው” በማለት ለንጉሡ ተናገረ።

1 ነገሥት 2