16. በዚያም ሰፈር የነበሩ እስራኤላውያን ዘምሪ ዐምፆ ንጉሡን መግደሉን እንደ ሰሙ፣ የሰራዊቱን አዛዥ ዖምሪን በዚያኑ ዕለት እዚያው ሰፈር ውስጥ በእስራኤል ላይ ማንገሣቸውን ዐወጁ።
17. ከዚያም ዖምሪና አብረውት ያሉት እስራኤላውያን ሁሉ ከገባቶን ወደ ላይ ወጥተው ቴርሳን ከበቡ።
18. ዘምሪ ከተማዪቱ መያዟን ሲያይ፣ ቤተ መንግሥቱ ውስጥ ወዳለው ግንብ ገብቶ በቤተ መንግሥቱ ላይ እሳት ለቀቀበትና በዚሁ ሞተ።
19. ይህ የሆነውም በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ክፉ ሥራ በመሥራትና በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድ፣ እንዲሁም ራሱ በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ ባደረገው ኀጢአት ምክንያት ነው።
20. ሌላው ዘምሪ በዘመኑ የፈጸመው ድርጊትና ያካሄደውም ዐመፅ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አደለምን?
21. ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ ከሁለት ተከፈለ፣ ይህም ግማሹ የጎናትን ልጅ ታምኒን ለማንገሥ ሲሆን፣ የቀረው ደግሞ ዖምሪን በመደገፍ ነበር።
22. ሆኖም የዖምሪ ተከታዮች ከጎናት ልጅ ከታምኒ ተከታዮች ይልቅ በረቱ፤ ስለዚህ ታምኒ ሞተ፤ ዖምሪም ነገሠ።
23. የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሠላሳ አንደኛው ዓመት፣ ዖምሪ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ዐሥራ ሁለት ዓመትም ገዛ፤ ከዚህም ውስጥ ስድስቱን ዓመት የገዛው በቴርሳ ሆኖ ነው።
24. እርሱም የሰማርያን ኰረብታ በሁለት መክሊት ጥሬ ብር ከሳምር ላይ ገዝቶ ከተማ ሠራባት፤ ስሟንም በቀድሞው የተራራዋ ባለቤት በሳምር ስም ሰማርያ ብሎ ጠራት።
25. ይሁን እንጂ ዖምሪ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ ከእርሱ አስቀድሞ ከነበሩትም ይልቅ የበለጠ ኀጢአት ሠራ።