27. ናዳብና መላው እስራኤል በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከበው ሳሉ፣ ከይሳኮር ነገድ የተወለደው የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐምፆ በመነሣት ናዳብን በገባቶን ገደለው።
28. ባኦስ ናዳብን የገደለውና በእግሩ ተተክቶ የነገሠው፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው።
29. ወዲያውኑ እንደ ነገሠም የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ። እግዚአብሔር በሴሎናዊው ባሪያው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረው፣ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀር፣ ሁሉንም አጠፋቸው፤
30. ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን ለቊጣ በማነሣሣቱ ነው።
31. ሌላው በናዳብ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ እርሱም ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?
32. አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።
33. የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በቴርሳ ከተማ፣ በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ሃያ አራት ዓመትም ገዛ።
34. በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ።