1 ነገሥት 15:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ።

13. አስጸያፊውን የአሼራ ምስል ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው።

14. አሳ የማምለኪያ ኰረብታዎችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር የተገዛ ነበር።

15. አባቱና እርሱ ለእግዚአብሔር የቀደሱትን ብርና ወርቅ እንዲሁም ዕቃዎችን አምጥቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት አስገባ።

16. አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

17. የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ይሁዳን ለመውጋት ወጣ፤ ከዚያም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት።

18. አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በታማኝ ሹማምቱ እጅ በደማስቆ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሀዳድ ላከው።

19. እንዲህም አለ፤ “በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ አሁንም በእኔና በአንተ መካከል ይኑር፤ እነሆ፣ የብርና የወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ወደ መጣበት እንዲመለስ፣ ሄደህ ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ።”

20. ቤንሀዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ጌንሳሬጥን በሙሉ ድል አደረገ።

21. ባኦስም ይህን ሲሰማ፣ በራማ የጀመረውን የምሽግ ሥራ አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ።

22. ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ አስቀምጦት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ ንጉሡም በዚሁ ምጽጳንና በብንያም ውስጥ ጌባን ሠራ።

1 ነገሥት 15