1 ነገሥት 15:1-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ በይሁዳ ነገሠ፤

2. በኢየሩሳሌም ሆኖ ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

3. እርሱም አባቱ ከእርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም።

4. ነገር ግን ከእርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው።

5. ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም።

6. አብያም በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።

7. ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር።

8. አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

9. የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤

10. በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ አያቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

11. አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።

12. የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ።

13. አስጸያፊውን የአሼራ ምስል ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው።

14. አሳ የማምለኪያ ኰረብታዎችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር የተገዛ ነበር።

15. አባቱና እርሱ ለእግዚአብሔር የቀደሱትን ብርና ወርቅ እንዲሁም ዕቃዎችን አምጥቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት አስገባ።

16. አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

17. የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ይሁዳን ለመውጋት ወጣ፤ ከዚያም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት።

18. አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በታማኝ ሹማምቱ እጅ በደማስቆ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሀዳድ ላከው።

1 ነገሥት 15