1. እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደ ሴኬም ስለ ሄዱ፣ ሮብዓም ወደዚያው ሄደ።
2. የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን በሰማ ጊዜ፣ ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ ከሚኖርበት ከግብፅ ተመልሶ መጣ።
3. ስለዚህም ወደ ኢዮርብዓም ላኩበት፤ እርሱና መላው የእስራኤል ጉባኤም ወደ ሮብዓም መጥተው፣
4. “አባትህ ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን አሁን የአባትህን የጭካኔ አገዛዝ የጫነብንንም ከባድ ቀንበር ብታቀልልን እንገዛልሃለን” አሉት።
5. ሮብዓምም፣ “እንግዲያውስ ሂዱ፤ ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ሄዱ።
6. ከዚያም ሮብዓም አባቱ ሰሎሞን በሕይወቱ ሳለ ካገለገሉት ሽማግሌዎች ጋር ተማከረ፤ “ለዚህ ሕዝብ ምን መልስ እንድሰጥ ትመክሩኛላችሁ?” አላቸው።
7. እነርሱም፣ “ዛሬ አንተ ለዚህ ሕዝብ አገልጋይ ብትሆን፣ ብትገዛለትና ደስ የሚያሰኝ መልስ ብትሰጠው፣ ምንጊዜም የአንተ አገልጋይ ይሆናል” ብለው መለሱለት።
8. ሮብዓም ግን ሽማግሌዎቹ የሰጡትን ምክር ንቆ፣ አብሮ አደግ የሆኑትንና እርሱን የሚያገለግሉትን ወጣቶች፣
9. “ሐሳብ ለማግኘት፣ የእናንተስ ምክር ምንድን ነው? ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች ምን መልስ እንስጥ?” ሲል ጠየቃቸው።
10. ወጣት አብሮ አደጎቹም፣ እንዲህ አሉት፣ “ ‘አባትህ ከባድ ቀንበር ጫነብን፣ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ላሉህ ለእነዚህ ሰዎች፣ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤
11. አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን ከዚያ ይብስ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ’ በላቸው!” አሉ።
12. ንጉሡ፣ “በሦስተኛው ቀን ተመልሳችሁ ኑ” ብሎአቸው ስለ ነበር፣ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም ተመልሰው መጡ።
13. ንጉሡም በሽማግሌዎቹ የተሰጠውን ምክር ትቶ፣ ሕዝቡን የሚያስከፋ መልስ ሰጣቸው፤
14. ወጣቶቹ የሰጡትን ምክርም ተቀብሎ፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደባችሁ፤ እኔ ደግሞ ከዚያ ይብስ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገረፋችሁ፣ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው።
15. እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአኪያ አማካይነት ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም የተናገረው ቀድሞውኑ እግዚአብሔር የወሰነው ስለ ሆነ፣ መፈጸም ነበረበትና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16. እስራኤልም ሁሉ ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ ለንጉሡ እንዲህ በማለት መለሱ፤“ከዳዊት ምን ድርሻ አለን?ከእሴይስ ልጅ ምን የምናገኘው አለ?እስራኤል ሆይ፤ ወደየድንኳንህ ተመለስ፤ዳዊት ሆይ፤ እንግዲህ የገዛ ቤትህን ጠብቅ!ስለዚህም እስራኤላውያን ወደ ድንኳኖቻቸው ተመለሱ።
17. ሮብዓምም በይሁዳ ምድር በሚኖሩት እስራኤላውያን ላይ ገዥ ሆነ።
18. ንጉሥ ሮብዓም የጒልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤል ሁሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።