1 ነገሥት 11:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ንጉሥ ሰሎሞን ከፈርዖን ልጅ ሌላ ብዙ የባዕድ አገር ሴቶችን ማለትም ሞዓባውያትን፣ አሞናውያትን፣ ኤዶማውያትን፣ ሲዶናውያትን፣ ኬጢያውያትን አፈቀረ።

2. እነዚህም እግዚአብሔር እስራኤላውያንን፣ “ልባችሁን ወደ አማልክታቸው በርግጥ ይመልሱታልና ከእነርሱ ጋር መጋባት የለባችሁም” ካላቸው አሕዛብ ወገን ነበሩ፤ ሆኖም ሰሎሞን ከእነዚሁ ጋር ፍቅሩ ጠና።

3. እርሱም ከነገሥታት የተወለዱ ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት፤ ሚስቶቹም ልቡ ወደ ሌላ እንዲያዘነብል አደረጉት።

4. ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ሚስቶቹ ልቡን ወደ ሌሎች አማልክት መለሱት፤ የአባቱ የዳዊት ልብ እንደ ተገዛ ሁሉ፣ በፍጹም ልቡ ለአምላኩ ለእግዚአብሔር አልተገዛም።

5. ሰሎሞንም የሲዶናውያንን ሴት አምላክ አስታሮትን፣ አስጸያፊውን የአሞናውያንን አምላክ ሚልኮምን ተከተለ።

6. ስለዚህ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም እግዚአብሔርን እስከ መጨረሻው አልተከተለም።

1 ነገሥት 11