1. እኔ ነጻ ሰው አይደለሁምን? ሐዋርያስ አይደለሁምን? ጌታችንን ኢየሱስን አላየሁትምን? እናንተስ በጌታ የድካሜ ፍሬዎች አይደላችሁምን?
2. ለሌሎች ሐዋርያ ባልሆን እንኳ ለእናንተ ግን በርግጥ ሐዋርያ ነኝ፤ ምክንያቱም በጌታ የሐዋርያነቴ ማኅተም እናንተ ናችሁ።
3. ለሚመረምሩኝ የምሰጠው መልስ ይህ ነው።
4. ለመሆኑ፣ የመብላትና የመጠጣት መብት የለንምን?
5. እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት፣ እንደ ጌታ ወንድሞችና እንደ ኬፋ ሁሉ፣ እኛስ አማኝ ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንምን?
6. ወይስ ጥረን ግረን መኖር ያለብን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?
7. ለመሆኑ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋ እየጠበቀ የከብቱን ወተት የማይጠጣ ማን ነው?