1 ቆሮንቶስ 4:7-18 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ለመሆኑ፣ አንተን ከሌላው እንድትበልጥ ያደረገህ ማን ነው? ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ?

8. አሁንስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችኋል! ሀብታምም ሆናችኋል! ከእኛም ተለይታችሁ ነግሣችኋል! በርግጥ ብትነግሡማ እኛም ከእናንተ ጋር በነገሥን ነበር፤

9. ምክንያቱም እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያቱን፣ ሞት እንደ ተፈረደባቸው ሰዎች ከሰው ሁሉ መጨረሻ ያሰለፈን ይመስለኛል፤ ለዓለም ሁሉ፣ ለመላእክትም ለሰዎችም ትርኢት ሆነናል።

10. እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ጥበበኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፤ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፤ እኛ ግን የተዋረድን ነን።

11. እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፤ እንጠማለን፤ እንራቈታለን፤ እንደ በደባለን፤ ያለ መጠለያ እንንከራተታለን፤

12. በገዛ እጃችን እየሠራን እንደክማለን። ሲረግሙን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤

13. ስማችንን ሲያጠፉ መልካም እንመልሳለን። እስከ አሁን ድረስ የዓለም ጒድፍ፣ የምድር ጥራጊ ሆነናል።

14. ይህን የምጽፍላችሁ እንደ ተወደዳችሁ ልጆቼ አድርጌ ልመክራችሁ እንጂ ላሳፍራችሁ ብዬ አይደለም።

15. ምንም እንኳ በዐሥር ሺህ የሚቈጠሩ ሞግዚቶች በክርስቶስ ቢኖሯችሁም፣ ብዙ አባቶች ግን የሏችሁም፤ በወንጌል አማካይነት በክርስቶስ ኢየሱስ ወልጄአችኋለሁና።

16. ስለዚህ እኔን እንድትመስሉ እለምናችኋለሁ።

17. እንግዲህ በጌታ የተወደደውንና የታመነውን ልጄን ጢሞቴዎስን የላክሁላችሁ በዚህ ምክንያት ነው፤ እርሱም በየስፍራው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ከማስተምረው ትምህርት ጋር የሚስማማውን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን የሕይወት አካሄዴን ያሳስባችኋል።

18. ከእናንተ አንዳንዶቹ ወደ እናንተ የማልመጣ መስሎአቸው ታብየዋል፤

1 ቆሮንቶስ 4