1 ሳሙኤል 8:10-22 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፣ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ።

11. እንዲም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ።

12. አንዳንዶቹን ሻለቆችና አምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፣ የቀሩትን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል፤

13. ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቶ ቀማሚ፣ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል።

14. ከእርሻችሁ፣ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለ ሟሎቹ ይሰጣቸዋል።

15. ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለ ሟሎቹ ይሰጣቸዋል።

16. ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ለራሱ ያደርጋቸዋል።

17. ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተ ራሳችሁም ባሪያዎቹ ትሆናላችሁ።

18. ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ወዳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን እግዚአብሔር አይመልስላችሁም።”

19. ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እምቢ በማለት፤ እንዲህ አሉ፤ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን፤

20. እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፣ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።”

21. ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ በእግዚአብሔር ፊት ተናገረው።

22. እግዚአብሔርም፣ “አድምጣቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው።ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፣ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።

1 ሳሙኤል 8