1. ፍልስጥኤማውያን የእግዚአብሔርን ታቦት ከማረኩ በኋላ፣ ከአቤንኤዘር ወደ አሽዶድ ወሰዱት።
2. ከዚያም ወደ ዳጎን ቤተ ጣዖት አግብተው፣ በዳጎን አጠገብ አኖሩት።
3. የአሽዶድም ሰዎች በማግስቱ ማለዳ ተነሥተው ሲመለከቱ እነሆ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት። ከዚያም አንሥተው ወደ ቦታው መለሱት።
4. በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ተነሥተው ሲመለከቱ፣ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት፣ መሬት ላይ በግንባሩ ተደፍቶ ነበር፤ ራሱና እጆቹ ተሰባብረው በደጃፉ ላይ የወደቁ ሲሆን፣ የቀረው ሌላው አካሉ ብቻ ነበር።
5. የዳጎን ካህናትም ሆኑ ሌሎች በአሽዶድ ወዳለው የዳጎን ቤተ ጣዖት የሚገቡ ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ እግራቸው ደጃፉን እንዳይረግጥ ተራምደው የሚያልፉት በዚሁ ምክንያት ነው።
6. የእግዚአብሔር እጅ በአሽዶድ ሕዝብና በአካባቢዋ ላይ ጠነከረ፤ እርሱም ጥፋት አመጣባቸው፤ በዕባጭም መታቸው።
7. የአሽዶድ ሰዎች ይህን ባዩ ጊዜ፣ “እጁ በእኛና በአምላካችን በዳጎን ላይ ጠንክሮአልና የእስራኤል አምላክ ታቦት በእኛ ዘንድ መቈየት የለበትም” አሉ።