1 ሳሙኤል 23:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ “እነሆ፤ ፍልስጥኤማውያን በቅዒላ ላይ ጦርነት ከፍተው፣ ዐውድማውን እየዘረፉት ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት።

2. እርሱም፣ “እነዚህን ፍልስጥኤማውያን ሄጄ ልምታን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “ሂድ፤ ፍልስጥኤማውያንን ምታ፤ ቅዒላንም አድናት” ብሎ መለሰለት።

3. የዳዊት ሰዎች ግን፣ “እዚሁ በይሁዳ ምድር እያለን እየፈራን ነው፤ የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመውጋት ወደ ቅዒላ የምንሄድ ከሆነማ ምን ያህል የሚያስፈራ ነው?” አሉት።

4. ዳዊት እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥ፣ ወደ ቅዒላ ውረድ” አለው።

5. ስለዚህ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ ቅዒላ ሄደው፣ ፍልስጥኤማውያንን ወጉ፤ እንስሶቻቸውን ማርከው ወሰዱ፤ በፍልስጥኤማውያን ላይ ከባድ ጒዳት አደረሱ፤ ዳዊትም የቅዒላን ሕዝብ ታደገ።

6. የአቢሜሌክ ልጅ አብያታር ወደ ቅዒላ ወደ ዳዊት በሸሸ ጊዜ፣ ኤፉዱን ይዞ ወርዶ ነበር።

7. ሳኦል የዳዊትን ወደ ቅዒላ መሄድ በሰማ ጊዜ፣ “ዳዊት መዝጊያና የብረት መወርወሪያ ወዳላት ከተማ መግባቱ፣ ራሱን በራሱ እንደ ማሰር ስለ ሆነ፣ ይህን ሰው እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ሰጥቶኛል” አለ።

1 ሳሙኤል 23