1. ከዚህ በኋላ “እነሆ፤ ፍልስጥኤማውያን በቅዒላ ላይ ጦርነት ከፍተው፣ ዐውድማውን እየዘረፉት ነው” ብለው ለዳዊት ነገሩት።
2. እርሱም፣ “እነዚህን ፍልስጥኤማውያን ሄጄ ልምታን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፣ “ሂድ፤ ፍልስጥኤማውያንን ምታ፤ ቅዒላንም አድናት” ብሎ መለሰለት።
3. የዳዊት ሰዎች ግን፣ “እዚሁ በይሁዳ ምድር እያለን እየፈራን ነው፤ የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ለመውጋት ወደ ቅዒላ የምንሄድ ከሆነማ ምን ያህል የሚያስፈራ ነው?” አሉት።
4. ዳዊት እንደ ገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “ፍልስጥኤማውያንን በእጅህ አሳልፌ ስለምሰጥ፣ ወደ ቅዒላ ውረድ” አለው።