2. ሳኦልና እስራኤላውያን ተሰብስበው፣ በዔላ ሸለቆ ሰፈሩ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ለመግጠም ቦታ ቦታቸውን ያዙ።
3. ሸለቆ በመካከላቸው ሆኖ ፍልስጥኤማውያን አንዱን ኰረብታ እስራኤላውያን ደግሞ፣ ሌላውን ኰረብታ ያዙ።
4. ከጌት የመጣ ቁመቱ ከዘጠኝ ጫማ በላይ የሆነ፣ ጎልያድ የተባለ አንድ ጀግና ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጣ።
5. እርሱም ከናስ የተሠራ የራስ ቍር ደፍቶ፣ ክብደቱ አምስት ሺህ ሰቅል የሆነ የናስ ጥሩር ለብሶ ነበር።
6. በእግሮቹ ላይ የናስ ገምባሌ አድርጎ፣ በጫንቃው ላይ ደግሞ የናስ ጭሬ ይዞ ነበር።
7. የጦሩም ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የወፈረ፣ የጦሩም ብረት ስድስት መቶ ሰቅል ያህል የሚመዝን ነበር፤ ጋሻ ጃግሬውም ከፊት ከፊቱ ይሄድ ነበር።
8. ጎልያድ ቆሞ ለተሰለፈው የእስራኤል ሰራዊት እንዲህ ሲል ጮኾ ተናገረ፤ “ለውጊያ ተሰልፋችሁ መውጣታችሁ ስለምንድን ነው? እኔ ፍልስጥኤማዊ፣ እናንተም የሳኦል አገልጋዮች አይደላችሁምን? አንድ ሰው ምረጡና እኔ ወደ አለሁበት ይውረድ፤
9. ከእኔ ጋር ሊዋጋና ሊገድለኝ ከቻለ፣ እኛ ባሪያዎቻችሁ እንሆናለን፤ እኔ ባሸንፈውና ብገድለው ግን እናንተ ባሪያዎቻችን ትሆናላችሁ፤ ትገዙልናላችሁ።”
10. ከዚያም ፍልስጥኤማዊው፣ “ዛሬ የእስራኤልን ሰራዊት እገዳደራለሁ፤ እንዋጋ ዘንድ ሰው ስጡኝ” አለ።
11. ሳኦልና እስራኤላውያን ሁሉ የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም።
12. ዳዊት በይሁዳ የቤተ ልሔሙ ሰው የኤፍራታዊው የእሴይ ልጅ ነበር። እሴይ ስምንት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ በሳኦልም ዘመን ያረጀና ዕድሜው የገፋ ሰው ነበር።